Phone:

666 888 0000

ኢሜይል:

contact@h4peace.org

ለሰላምና ለአንድነት ድልድዮች እንገንባ

በታሪካችን ያልታየ አሳዛኝ ምእራፍ
ሥር የሰደደ የብሄር መለያየት በአንድ ወቅት በወንድማማችነት እና በእህትማማችነት ለዘመናት በኖሩ ማህበረሰቦች መካከል ከፍተኛ አለመተማመን እንዲፈጠር አድርጓል። ይህም ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ መጠን አሳዛኝ ወደ ሆነ ጦርነትና ውድመትም አስገብቷል። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ሞተዋል፣ ቆስለዋል፣ ተሰቃይተዋል፣ ተደፍረዋል፣ ተፈናቅለዋል። አደጋው ዛሬም እንደቀጠለ ነው።
በተዋንያን የተባባሰ ችግር
አደጋው የተቀሰቀሰውና የተባባሰው ለጥቅማቸው ሲሉ ከውስጥም ሆነ ከውጪ በሚንቀሳቀሱ ሃይሎች ነው። በሚያሳዝን ሁኔታ እነዚህ ተዋናይ ሃይሎች አሁንም ችግሩ በእርቅ እንዳይፈታ እንቅፋት እየሆኑ ይገኛሉ። ያለ ቆራጥ የተቆርቋሪ ዜጎች ጣልቃገብነትና ተሳትፎ የተገባበት የእርስ በርስ መጠፋፋት ዘላቂ መፍትሄ ሊያገኝ አይችልም። ይህ መቆም አለበት።
በጎ ፈቃደኛ ይሁኑ!
አገርዎንና ህዝብዎን መርዳት ይችላሉ። የተስፋ ለሰላም የበጎ ፈቃደኛ በመሆን በሰላምና እርቅ ጥረቶች ላይ ተጨባጭ አስተዋጾ ያድርጉ። ማህበረሰቦችን በማገናኘት፣ ውይይትን በማጎልበት፣ ሰላም ያላቸው ክልሎች እና አንድነትዋ የጠነከረ ኢትዮጵያን ለመገንባት ጊዜዎን፣ ጉልበትዎንና እውቀትዎን ያበርክቱ። የጋራ ስምምነትና መግባባት የሰፈነባት አገር መፍጠር እንችላለን።
የሰላም ተልእኳችን

ሰላም የሞላባት ነገይቱ ለመፍጠር የሚደረጉ የማቀራረብ ጥረቶች

ተስፋ ለሰላም ከአማራ እና ከትግራይ ማህበረሰቦች የተውጣጡ ኢትዮጵያውያን እና በትውልደ ኢትዮጵያውያን በጋራ ያደረጉት የጥረት ውጤት ነው። የጋራ ጭንቀታችን የሚመነጨው በነዚህ ለዘመናት የቆየው ታሪክና ትውፊት ያላቸው ሁለት ወንድማማች ህዝቦች መካከል ግንኙነታቸውን ካበላሸው ከባድ ጠላትነትና ግጭት ነው። ተቀዳሚ አላማችን ግልፅ ነው፡ ከቅርብ አመታት ወዲህ በአማራ እና በትግራይ ማህበረሰቦች መካከል እየተባባሰ የመጣውን አሳሳቢ የሆነ ጠላትነት በንቃት መፍታትና ማክሸፍ ነው። ወደ ክልላችን ሰላምና መረጋጋት እንዲመለስም መንገድ ለመክፈት ቆርጠን ተነስተናል።
Unifying Efforts for a Peaceful Future
ከዚህ በፊት ታይቶ የማያውቅ ፈተና

በግጭቶች የተበላሹ ታሪካዊ ትስስሮች

የተስፋ ለሰላም መሰረቱ በአማራ እና በትግራይ ማህበረሰቦች መካከል ከተፈጠረው ያልተለመደ ጠላትነት የተነሳ ነው። እነዚህ ሁለት ማህበረሰቦች የተጠላለፉ የህልውና፣ የባህል አንድነት፣ የጋራ እምነትና ሃይማኖታዊ ተግባራት ያዛመደ ጥልቅ የሆነ ታሪክ አላቸው። ይህ ጠላትነት በፖለቲካ ልሂቃን ላይ ብቻ የተገደበ ሳይሆን በሌላው ህዝብ ህይወት ውስጥም ዘልቆ በመግባቱ ጉዳዩን ይበጥ አሳሳቢ አድርጎታል። ይህ ግጭት በሁለቱም ማህበረሰቦች ከፍተኛ የሰው ሰቆቃና የንብረት ውድመት በማድረስ ሀገሪቱን ለከፋ የፖለቲካ ቀውስ ዳርጓል። በታሪካችን ከየትኛውም ጊዜ በተለየ የውጭ ኃይሎች ተሳትፎ በሕዝባችንና በአገራችን ላይ የሚደርሰውን አደጋ የበለጠ አጠናክሮታል።
አንድ ወጥ የሆነ የሰላም መንገድ

ለፖለቲካዊ መፍትሄዎች ድልድይ እንገንባ

የተስፋ ለሰላም ዋና ዓላማ ታሪካዊ ቅርበት ባላቸው በአማራና በትግራይ ማህበረሰቦች መካከል እየታየ ያለውን ጥላቻ እና ግጭት ማስቆም ነው። ምኞታችን እርቅ ከማምጣት በላይ የዘለቀ ነው። አላማችን ሁለቱ ማህበረሰቦችና መሪዎቻቸው ፖለቲካዊ እና ሌሎች ልዩነቶቻቸውን በሰላማዊ መንገድ፣ በውይይት፣ በድርድርና በህጋዊ ሂደቶች ለመፍታት የሚያስችል ሰላማዊ የፖለቲካ ምህዳር እዲፈጥሩ ማድረግ ነው።

የዚህ ቀውስ መነሻና መፍትሄው ፖለቲካዊ ይዘት ያለው መሆኑን ተስፋ ለሰላም ይገነዘባል። ይሁንና ሃላፊነቱን በገለልተኝነት ከመወጣት ባለፈ ለፖለቲካ ስልጣንም ሆነ ለሌላ አላማ የመቆም ፍላጎት የለውም ። አላማችን በአማራና በትግራይ ማህበረሰቦች ሰላም እንዲሰፍንና ግንኙነታቸው ጤናማ እንዲሆን ገንቢ ሚና መጫወት ነው። ስብስባችን ቋሚ አደረጃጀት የሌለው፣ ውስን አጀንዳ የሚያራምድ እና ህጋዊ እውቅና የማያስፈልገው ቢሆንም፣ የተነሳንለት አላማ ታላቅ እና ህዝባዊ ነው።
የአንድነት ጥሪ

ብሄራዊ እርቅ ለጠንካራ ኢትዮጵያ

ተልእኳችን በዋነኛነት በትግራይ እና በአማራ ማህበረሰቦች መካከል ያለውን ችግር የሚፈታ ቢሆንም፣ እነዚህ ተግዳሮቶች ከሰፊው አገራዊ ጉዳይና ከመላው የኢትዮጵያውያን ፍላጎትና ጥቅም ጋር የተቆራኙ መሆናቸውን እንገነዘባለን። የተልዕኳችን ስኬት በሀገሪቱ ውስጥ ባሉ ማህበረሰቦች ንቁ ተሳትፎና ድጋፍ ላይ የተመሰረተ ነው። ስለሆነም፣ በእነዚህ ሁለት ማህበረሰቦች መካከል እየተፈጠረ ያለው የጠላትነት ስሜት በአገራዊና ክልላዊ መረጋጋት ላይ ስላለው ሰፊ አንድምታ ያለንን ግንዛቤ የሚጋሩትን የሌሎች ብሄሮች ተወላጆች ጭምር የሚያካትት ይሆናል። በመተባበርም የበለጠ ፍትሃዊ የሆነች፣ አንድነትና ሰላም የሰፈነባት ኢትዮጵያን በትጋት መገንባት እንችላለን።