Phone:

666 888 0000

ኢሜይል:

contact@h4peace.org

ጦርነትና ውድመት ይቁም! – የሰላም ለተስፋ ስብስብ ጥሪ

ታህሳስ 29 ቀን 2016 ዓ.ም

ጦርነትና ውድመት ይቁም!

የሰላም ለተስፋ ስብስብ ጥሪ

ኢትዮጵያ ከ2012 ዓ.ም. ጀምሮ በታሪኳ አይታው በማታውቀው እጅግ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ በማለፍ ላይ ነች። ከመቶ ሃያ ሚሊዮን በላይ በሆነው ህዝቧ የአፍሪካን ህዝብ 10 በመቶ ድርሻ ያላት ይህች ጥንታዊት አገር ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ በሚታትሩ የውስጥና የውጭ ሀይሎች በቀውስና በብጥብጥ እየተመሰቃቀለች ትገኛለች። በህዳር 2015 ዓ.ም. የተፈረመው የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ዘላቂ ሰላም ለማምጣት በሚያስችል አግባብ ባለመፈጸሙ ምክንያት ፈንጥቆ የነበረው ተስፋ ልብ በሚሰብር ሁኔታ የመደናቀፍ አደጋ ገጥሞታል። ስምምነቱ ከተፈረመ ከአመት በዃላም እንኳ በሰሜኑ የአገራችን ክፍል በየእለቱ ብዙ ህዝብ በረሃብና በመሰረታዊ የጤና አገልግሎት እጦት እየረገፈ፣ ከቀየው የተፈናቀለው ህዝብም እስካሁን ወደ መኖርያ ቦታው ሳይመለስ በመቅረቱ በስቃይና በመከራ ውስጥ እያለፈ ይገኛል።

ከፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት በፊት በሰሜኑ የአገራችን ክፍል በተካሄደው ጦርነት ምክንያት በዋነኛነት በትግራይ፣ እንዲሁም በአማራና በአፋር በአንዳንድ ምንጮች ግምት ከሚሊዮን በላይ የተገመቱ የታጠቁና ያልታጠቁ ሲቪል ዜጎች በሞት መቀጠፋቸው ይታወቃል። በጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ የሚመራው አገዛዝ ዋና መለያ ባህሪው በሆነው የጥፋት ስልት አማካይነት የትግራይ ህዝብ ለሁለት አመታት በሙሉ ከበባ ውስጥ እንዲሆን፣ ከአለም እንዲነጠልና ቃላት በማይገኝለት ሰቆቃና ጥፋት እንዲማቅቅ መደረጉ ሳያንስ ከሰላም ስምምነቱ በኋላም በብዙ ማህበራዊ፣ ኤኮኖሚያዊ፣ ሰብአዊና ፖለቲካዊ ቀውሶች ውስጥ እንዲያልፍ እየተደረገ ነው።

በትግራይ የተከሰተው አጠቃላይ ውድመት በአሁኑ ጊዜ በተመሳሳይና በአሳዛኝ ሁኔታ በአማራ ክልል ውስጥም በመደገም ላይ ይገኛል። የአማራ ህዝብ ያለማሰለስ እየተካሄደበት ባለው የጭፍጨፋና የድሮን ድብደባ ከፍተኛ ስቃይ ውስጥ ገብቷል። ልክ በትግራይ ህዝብ ላይ ሲሆን እንደታየው ሁሉ የአማራ ህዝብም ከሌላው አለም እንዲነጠል ተደርጎ በፈንጂ እቶን እየተቃጠለ፣ በጥይት አረር እየተቆላ፣ በረሃብና በህክምና አገልግሎት ንፍገትና ውድመት ጭምር እየረገፈ ነው። ይህም አልበቃ ያለው አገዛዙ በንጹሃን ዜጎች ላይ በዘፈቀደ የጅምላ አፈሳ፣ በአፈናና እስር፣ እንዲሁም በንብረት ዘረፋና ውድመት እጅግ አስከፊ በደልና ወከባ በህዝቡ ላይ ማድረሱን ቀጥሏል። ይህ በአስር ሚሊዮኖች የሚቆጠረው የአማራ ህዝብ ወደ መከራ አረንቋ እንዲገባ ሲደረግ በአይናችን ለመመልከት ተገደናል።

በሚገርም ሁኔታ ከ1977 ዓ.ም. በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በትግራይና በአማራ ክልል ዜጎች በረሃብ ምክንያት መሞት ጀምረዋል። ቀድሞ ሊደርስላቸው ይገባ የነበረው ማእከላዊ መንግስት ሃላፊነቱን መወጣት ተስኖት ዜጎች በረሃብ ምክንያት እየሞቱ መሆናቸውን በመካድ መከራከርን መርጧል። ይህ ሁሉ የሚያሳየው የነዚህ ሁለት ክልሎች ህዝብ በወቅቱ አገዛዝ ምን ያህል ህልውናው አደጋ ውስጥ እንደወደቀ ነው።

የኢትዮጵያ ማእከላዊ መንግስት የዜጎችን ደህንነት ከማስጠበቅ ሃላፊነቱ በተቃራኒ በክልሎች፣ በብሄሮችና በማህበረሰቦች መካከል ሆን ብሎ በሚቆሰቁሰው ጥላቻና ግጭት ምክንያት ራሱ የብጥብጥ ምንጭ ሆኖ ተከስቷል። ይህ ድርጊቱም በአማራና በትግራይ ማህበረሰቦች መካከል ቁርሾዎችን በመቆስቆስና ውጥረት በመፍጠር ሲከሰት እንደቆየው ሁሉ አሁንም በተመሳሳይ ድርጊቱ እንደቀጠለበት በብዙ ማስረጃዎች እየታየ ነው። ይህ ህዝብን ከህዝብ እያዋጉ የመቀጠል እጅግ አደገኛ ድርጊት በአስቸኳይ መቆም ይኖርበታል።

አገሪቱን እያደቀቃት በሚገኘው የጦርነት አዙሪት ምክንያት በየእለቱ እያሻቀበ ባለው የዋጋ ንረትና ከቁጥጥር ውጭ እየሆነ በመጣው የስራ አጥነት መስፋፋት መረዳት እንደሚቻለው ኢትዮጵያ ወደ አስከፊ የኤኮኖሚ ውድቀትና ቀውስ ውስጥ በከፍተኛ ፍጥነት እየገባች ትገኛለች። በመላ አገሪቱ የረሃብ ወረርሽኝ ተስፋፍቷል። የዜጎች እንቅስቃሴም በሰላምና ደህንነት እጦት ምክንያት በእጅጉ ታግቷል። አገዛዙ በተደጋጋሚ የብድር ወለድ መክፈል ተስኖት አለም አቀፍ የእዳ ግዴታዎቹን መወጣት የማይችልበት ደረጃ ላይ ደርሷል። በዚህ ሁሉ መካከል ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እያቀነቀኑት የሚገኘው የባህር በር ጥያቄ በአገሪቱና በአካባቢው አዲስ ስጋትና ውጥረት እየፈጠረ ነው። በቅርቡ በአገዛዙና በኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት መካከል የተሞከረው የሰላም ስምምነት ሳይሳካ መቅረቱም አሁንም በጥፋት አዙሪት እየቀጠልን መሆኑ ሌላ ማሳያ ነው።

ተስፋ ለሰላም በሁለቱ አብዝሃ ህዝብ ባላቸው በአማራና በኦሮሚያ፣ እንዲሁም በመላው አገሪቱ እየተካሄዱ ያሉት አውዳሚ ጦርነቶችና ልዩ ልዩ ግጭቶች በአስቸኳይ እንዲቆሙ ካልተደረገ በስተቀር የአገሪቱ አጠቃላይ ህልውና በአጭር ጊዜ ወደ ከፋ አደጋ ሊገባ ይችላል የሚል ስጋት አለው። ኢትዮጵያ በእንዲህ አይነት የጦርነት አዙሪት ተዘፍቃ መቀጠሏ ለጉዳዩ ዋና ባለቤት ለኢትዮጵያ ህዝብ ብቻ ሳይሆን ለአለም አቀፉ ማህበረሰብም አሳሳቢ ሊሆን ይገባል። አለም አቀፉ ማህበረሰብ ከፍተኛ ታሪካዊና ስትራተጂያዊ ትርጉም ለያዘችውና የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ ለሆነችው አገር ለኢትዮጵያ ተገቢ ትኩረት ሊሰጥ ይገባል እንላለን። ይኸውም ጉዳዩ በሚመለከታቸው ሃይሎች ላይ ተገቢ ጫና ማድረግና በረሃብ ለተጠቁ አካባቢዎችና ህዝቦች የሰብአዊ እርዳታ በአስቸኳይ እንዲደርስ የማድረግ ሃላፊነቱን ይወጣ ዘንድ በአንክሮ እናሳስባለን። ይህን አስቸኳይ እርምጃ መውሰድ ያለመቻል ግን በኢትዮጵያ ህዝብ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካና በመላው አለም ህዝብ ፊት የሚያስጠይቅ ይሆናል። በአጠቃላይ በአሁኑ ወቅት አገሪቱ የምትገኝበትን አስቸጋሪ ሁኔታ ወደ በጎ አቅጣጫ ለመቀየር የኢትዮጵያ ህዝብም ሆነ የአለም አቀፉ ማህበረሰብ የጋራ ሃላፊነትና ርብርብ አስፈላጊ መሆኑን ስብስባችን ያስገነዝባል።

 

ተስፋ ለሰላም፣ ሰሜን አሜሪካ

ሰላም ለህልውናችን!

 

Search
Social Share