Phone:

666 888 0000

ኢሜይል:

contact@h4peace.org

የአገዛዙ ህዝብን ከህዝብ የማዋጋት ዳግም ሴራ ሊከሽፍ ይገባል!

የአገዛዙ ህዝብን ከህዝብ የማዋጋት ዳግም ሴራ ሊከሽፍ ይገባል!

ከተስፋ ለሰላም የተሰጠ መግለጫ

 

መጋቢት 23 ቀን 2016 ዓ.ም.

ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን መምጣት በኋላ በኢትዯጵያ ውስጥ በሺ የሚቆጠሩ ግጭቶች ተከስተዋል። በሰሜኑ የአገራችን ክፍልና በኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ ህዝብ ጨራሽ ጦርነቶች ተካሂደዋል፣ አሁንም በመካሄድ ላይ ይገኛሉ። ከአንድ አመት በፊት በፕሪቶርያው ስምምነት የቆመው የአማራና የአፋር ክልሎችን ጨምሮ በዋናነት በትግራይ በተካሄደው ጦርነት ብቻ በታሪካችን አይተነው በማናውቅ መጠን ከ1 ሚሊየን በላይ የሆነ ህዝብ እንደሞተና ከ4 ሚሊየን የበለጠ ህዝብ ከመኖሪያ ቀየው እንደተፈናቀለ ይገመታል።

እነዚህ ጦርነቶች የሚካሄዱት በዋናነት በመንግስትና በተቀናቃኝ የፖለቲካ ሀይሎች መካከል ቢሆንም ካለፈ ታሪካችን በተለየ መጠንና ሁኔታ ግጭቶቹ የህዝብ-ለህዝብ ግጭት የመሆን አዝማሚያ ሲይዙ ታይቷል። በተለይም በትግራይ በተካሄደው ጦርነት ለዘመናት በሰላማዊ ጉርብትናና በአንድ አገር ልጅነት አብረውና ተዛምደው የኖሩት የአማራና የትግራይ ህዝቦች ጐራ ለይተው የፍልሚያው አካል ሲሆኑ ታይተዋል። ለስብስባችን ተስፋ ለሰላም መመስረት ዋና ምክኒያት የሆነውም ይህ እውነታ የፈጠረው ከፍተኛ ስጋት ነው።

ተስፋ ለሰላም የተቋቋመው እነዚህ የረዥም ጊዜ የጋራ ታሪክ፣ ባህል፣ ስነ-ልቦናና ማንነት ተጋሪ የሆኑ ህዝቦች የትኛውም ዓይነት ቅራኔና ልዩነት በመካከላቸው ቢኖር ዳግም ጐራ ለይተው እርስ-በርስ መዋጋትና ደም መፋሰስ የለባቸውም የሚል ፅኑ እምነት በመያዝና የሁለቱን ህዝቦች ሰላማዊ ግንኙነት ለማጠናከር ነው።

የፕሪቶርያውን የሰላም ስምምነት መፈረም ከነጉድለቶቹም ቢሆን ጦርነቱን ከማስቆምም ባሻገር ለስብስባችን ዓላማ መሳካት በጐ ዕድል ሊፈጥር እንደሚችል በማሰብ ደግፈነዋል። በአማራና በኦሮሚያ ክልሎችም ተመሳሳይ የሰላም ስምምነቶች ሊፈረሙና ጦርነቶቹ ሊቆሙ ይችሉ ይሆናል የሚል ግምት ነበረን። ይሁንና የሰላሙ ጅማሮ የበለጠ እየተጠናከረና እየሰፋ ይሄዳል ብለን ተስፋ ባደረግንበት በአሁኑ ወቅት የትግራይንና የአማራን ህዝቦች ለዳግመኛ እልቂት የሚዳርግ ጦርነት እንደገና ሊያገረሽ የሚችልበት አደገኛ ሁኔታ እየተፈጠረ መሆኑን እየታዘብን ነው።

ቀድሞም ቢሆን አውዳሚው ጦርነት የተጀመረው የኃይለ-ቃል ልውውጥን ተከትሎ ነውና የሰሞኑ የመግለጫ ውዝግብም ሌላ የዕልቂት ድግስ ከፊታችን እየታሰበ እንደሆነ የሚያመላክት ስጋት ፈጥሮብናል። በስብስባችን እምነት እንኳንስ ሌላ ዙር ጦርነት መታሰቡና የበፊቱም ጦርነት እርባና-ቢስና ታሪካዊ ስህተት ነበር። የጦርነት አማራጭ የአገዛዙን የስልጣን ፍላጐት ለጊዜው ከማስጠበቅ አልፎ የማንኛውንም ህዝብ ጥቅምና ፍላጐት ሊያሳካ አይችልምና ምዕራፉ የተዘጋ አማራጭ ሊሆን ይገባዋል። ስለሆነም ህዝቡ-

አንደኛ፦ የሰሜኑን ህዝብ እርስ-በርስ እያዋጉ በማዳከም የስልጣን ዕድሜን ለማራዘም መሞከር የዘመኑ አገዛዝ አይነተኛ ዓላማ መሆኑን፤

ሁለተኛ፦ የሰሞኑ የኃይለ-ቃል ልውውጥ የአገዛዙን የሴራ ፍላጐት ለማሳካት ሲባል ሆን ተብሎ የተፈጠረ መሆኑን፤

ሶስተኛ፦ ካለፈው ስህተት ባለመማር በአገዛዙ የሴራ ወጥመድ ላይ ወድቆ ለሌላ ዙር ጦርነት መነሳሳት ሌላ የታሪክ ስህተት እንደሚሆን፤

አራተኛ፦ ከአሁን በኋላ በሁለቱ ህዝቦች ተሳትፎ የሚካሄድ ሌላ ዙር ጦርነት የባሰ የህዝብ ዕልቂት ከማስከተልም ባለፈ አጠቃላይ አገራዊና ህዝባዊ ህልውናን አደጋ ላይ የሚጥል መሆኑን፤

አምስተኛ፦ በሁለቱ ህዝቦች መካከል ያሉ አለመግባባቶች ሰላማዊ፣ ህጋዊና ዴሞክራሲያዊ ከሆነ መንገድ ውጭ በጦርነት ዘላቂ መፍትሄ ሊያገኙ እንደማይችሉ በመገንዘብ የአገዛዙን ሌላ ዙር ጦርነት የመጥመቅ ሴራ ህዝቡ በብቃት ሊያከሽፈው ይገባል።

ሁለቱን ህዝቦች እንወክላለን የምትሉ የፖለቲካ ኃይሎች፣ ጋዜጠኞች፣ ማህበራዊ አንቂዎችና ሌሎች ተሰሚነት ያላችሁ ስብስቦችና ግለሰቦች በእውነትም ለህዝብ ጥቅምና ደህንነት የምታስቡ ከሆነ የአገዛዙ የሴራ ሰለባ ወይንም ቅጥረኛ በመሆን ጦርነት ከመቀስቀስ ይለቅ በሁለቱ ህዝቦች መካከል ሰላማዊ ግንኙነት እንዲፈጠርና እንዲጠናከር ጠንክራችሁ መስራት ይገባቹሃል ብለን እናምናለን፣ አበክረንም እናስገነዝባለን:: ለማንኛውም ዓላማ ቢሆን ህዝብ ከህዝብ እንዲዋጋ መቀስቀስ የህዝብ ጠላትነት እንጅ ተቆርቋሪነት ሊሆን አይችልም። ህዝቡ ዛሬ ላይ የሚፈልገው ዘላቂ ሰላም፣ ዴሞክራሲና ልማት እንጅ ግጭትና ጦርነት አይደለም።

ስለሆነም የፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት ጉድለቶቹ ተሟልተው ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት በሚያስችል አግባብ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል እንጅ ስምምነቱን ጥሶ ወደ ሌላ አውዳሚ ጦርነት መግባት ተገቢ አይሆንም። ከማንም በላይ የአገሩ ባለቤት የሆነው ህዝብ “ከእንግዲህ ጦርነት በቃኝ!” በማለት የአገዛዙን ሴራና ደባ እንዲያከሽፍ ተስፋ ለሰላም ጥሪውንና ተማፅኖውን በዚህ አጋጣሚ ያቀርባል።

 

ተስፋ ለሰላም፣ ሰሜን አሜሪካ

ሰላም ለህልውናችን!

Search
Social Share