Phone:

666 888 0000

ኢሜይል:

contact@h4peace.org

በተደጋግሞ የሚነሱ ጥያቄዎች

ጥያቄዎች እና መልሶቻቸው

እናንተ እነማን ናችሁ? ለዚህ አላማ ምን አነሳሳችሁ? ልታሳኩት ያሰባችሁት ዋና አላማ ምንድን ነው?
  • እኛ የአማራና የትግራይ ተወላጅ የሆንን ሰዎች ባለፉት ጥቂት አመታት በሁለቱ ማህበረሰቦች መካከል የተፈጠረው የተካረረ ቅራኔና የእርስበርስ መጠፋፋት በእጅጉ ያሳሰበን ግለሰቦች ነን። በዚህ ስብስብ ወስጥ ያለን ሰዎች የህዝብም ሆነ የማንም የፖለቲካ ቡድን ውክልና የሌለን መሆናችን ሊታወቅ ይገባል።ወደዚህ ተነሳሽነት እንድንገባ ያስገደደንም በአሁኑ ጊዜ ህዝብን ከህዝብ እያጠፋፋ ያለው ቅራኔ ከወዲሁ ካልተገታ በሁለቱ ማህበረሰቦች ደህንነትና ህልውና ላይ እንዲሁም በአጠቃላይ በአገሪቱና በቀጣናው ደህንነት ዙሪያ ያሚያስከተለው አደጋ እጅግ ከፍተኛ መሆኑን በመረዳታችን ሲሆን ይሕንን የሰላም ሀሳብ ይዘን የመጣነውም አደጋው የበለጠ የከፋ እንዳይሆን ለማገዝ ነው።
  • ልናሳካው ያሰብነው አላማም በሁለቱ ማህበረሰቦች መካከል የተፈጠረው የወቅቱ ቅራኔ ሰላማዊና ህጋዊ በሆነ መንገድ እንዲሁም በሁለቱ ህዝቦች የውይይትና የድርድር ሂደት እንዲፈታ የዕርቅ መደላድል መፍጠርና በመካከላቸው ዳግም ጦርነት እንዳይከሰት የበኩላችንን አስተዋጽኦ ማበርከት ነው።
የስብስባችሁ ትኩረት ለምን በአማራና በትግራይ ማህበረሰቦች ላይ ብቻ ሆነ?
  • በሁለቱ ማህበረሰቦች ላይ ብቻ ያተኮርንበት ምክኒያት በታሪክ፣ በሃይማኖትና በተለያዩ ባህሎችና ማንነቶች የተጋመዱ ወንድማማች ማህበረሰቦች መካከል በአሁኑ ወቅት የሚታየው ቅራኔ አስተማማኝና ዘላቂ መፍትሄ ሳያገኝ በመቀጠሉ ነው። ቅራኔው በእስከአሁኑ የአገሪቱ ያለፈ ታሪክ ተከስቶ በማያውቅ መጠን ወደ የህዝብ ለህዝብ ቅራኔና መጠፋፋት ተሸጋግሯል። በኛ እምነት በአሁኑ ወቅት ይህ እየሆነ ያለው በሁለቱ ህዝቦች የእርስ በርስ ግጭትና መዳከም ተጥቃሚ እንሆናለን ብለው የሚያምኑ የውስጥና የውጭ የፖለቲካ ሃይሎች በመኖራቸው ነው። ይህ አደገኛ ሁኔታ በፍጥነት ተስተካክሎ የሁለቱ ህዝቦች ግኑኝነት ወደ በጎ ሁኔታ ካልተቀየረ ችግሩ ከሁለቱ ማህበረሰቦች አልፎ ለአጠቃላይ የአገሪቱ ህዝብና ለቀጣናው የህልውና አደጋ የሚያስከትል ይሆናል። ይህም እየሆነ ያለው በሂደት እየተጠራቀሙ የመጡት ቅራኔዎች በመባባሳቸው እና በተገቢው ጊዜ ተገቢ መፍትሄ ሳያገኙ በመቅረታቸው ነው። የኛ አላማ ከአማራና ከትግራይ ህዝብ ውጭ ያለውን ማህበረሰብ ማግለል ሳይሆን በሁለቱ ማህበረሰቦች መካከል ሰላም እንዲፈጠር ማገዝ ነው። በዚህ አጋጣሚ ይህ መድረክ በመርህም ሆነ በተግባር ከኦሮአማራ ስብስብ እጅጉን የተለየ መሆኑን ማሳወቅ እንወዳለን።
  • በትግራይና በአማራ ማህበረሰቦች መካከል በሚታየው መጠንም ባይሆን በሌሎች የአገሪቱ አካባቢዎችም ተመሳሳይ የህዝብ ለህዝብ ቅራኔዎች በየጊዜው እየተነሱና እያቆጠቆጡ መሆናቸውን እንገነዘባለን። ስለሆነም በሂደት በሌሎች የኢትዮጵያ ማህበረሰቦችም ዙርያ እየታዩ ያሉ እነዚህ ቅራኔዎችም እንዲረግቡ ተመሳሳይ ጥረቶችን ማካሄድ ተገቢ ነው ብለን እናምናለን። በዚህ ረገድ የሚመለከታቸው አካላቶችም የድርሻቸውን ማበርከት ይኖርባቸዋል።
በሁለቱ ማህበረሰቦች መካከል የተፈጠረው ይህ ግጭትና ጦርነት ለምን? እንዴት? በማንና በምን ምክኒያት ተፈጠረ ብላችሁ ታምናላችሁ?
  • በሁለቱ ማህበረሰቦች መካከል ለጦርነት የሚዳርግ ምንም አይነት መሰረታዊ ቅራኔ አለ ብለን አናምንም። ሁለቱ ማህበረሰቦች ለብዙ ዘመናት ተዛምደው፣ ተዋልደው፣ ተሳስረው የቆዩ ጥንታዊ ህዝቦች መሆናቸውን እናውቃለን።
  • በመካከላቸው አልፎ አልፎ የመጋጨት ሁኔታ ቢታይም፣ የነዚህ ግጭቶች መሰረታዊ መነሻዎች በጉዳዮች ላይ የተሳሳተ ግንዛቤ መኖር ነው ብለን እናምናለን። በዋናነት ግን የግጭቶቹ መንስኤዎች በሁለቱ ማህበረሰቦች በኩል የሚገኙ የፖለቲካ ሃይሎችና ልሂቃን ሲጭሩትና ሲያባብሱት የቆየና የተጠራቀመ ቅራኔ በመኖሩ እንደሆነ እንረዳለን።
  • በየዘመኑ የነበሩት መንግስታትና የፖለቲካ ሃይሎችም አሁን ለሚታዩት ግጭቶችና ችግሮች በተለያየ መጠን አስተዋጽኦ ያደረጉ መሆናቸውን እናምናለን። አሁን ባለንበት ዘመንም ይህ ችግር በውስጥና በውጭ ሃይሎች በተባባሰ፣ በተወሳሰበና በተካረረ መልኩ ስለቀጠለ ለከፍተኛ ቅራኔና ፍጅት እንዲሁም ለሁለቱ ማህበረሰቦች መቃቃርና መጋጨት የበለጠ አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑን ተገንዝበናል። ችግሩ በአሁኑ ወቅት ያለመፍትሄ ተባብሶ እንዲቀጥል የተደረገው በሁለቱ ህዝቦች የእርስ በርስ ግጭትና መዳከም ተጠቃሚ እንሆናለን ብለው የሚያምኑ እነዚህ የውስጥና የውጭ የፖለቲካ ሃይሎች በመኖራች ነው የሚል እምነት አለን።
ይህ ችግር በሰላማዊ መንገድ እንዴት ሊፈታ ይችላል? የማስፈጸሚያ ስልታችሁስ ምንድን ነው?
  • የአገሪቱ የፖለቲካ ሃይሎች ራሳቸውን ለዴሞክራሲ፣ ለእኩልነት፣ ለፍትህና በአጠቃላይም ለህዝብ ጥቅምና ደህንነት እስካስገዙ ድረስ በሰላማዊና ህጋዊ መንገድ የማይፈታ ችግር የለንም። አብዛኛዎቹ የዓለም አገሮች ውስብስብ የሆኑ ችግሮቻቸውን በሰላማዊ መንገድ እየፈቱ ጦርነትን ማስወገድ ችለዋል። የኢትዮጵያም ችግር በተመሳሳይ መንገድ ሊፈታ ይችላል ብለን እናምናለን።
  • ችግሩን በሰላማዊና ህጋዊ መንገድ ለመፍታት የምንከተለው የማስፈጸሚያ ሰልት ቀደም ሲል ባካሄድነው ውይይት እናስፈጽማቸዋለን ብለን በዝርዝር ባስቀመጥናቸው ክንውኖችና እነሱን ለማስፈጸም ባስቀመጥናቸው የማስፈጸሚያ ስልቶች አማካኝነት ይሆናል።
እንዴት ልረዳ እችላለሁ? እንዴት ላገኛቹህ እችላለሁ?
  • አገርዎንና ህዝብዎን መርዳት ይችላሉ። የተስፋ ለሰላም የበጎ ፈቃደኛ በመሆን በሰላምና እርቅ ጥረቶች ላይ ተጨባጭ አስተዋጾ ያድርጉ። ማህበረሰቦችን በማገናኘት፣ ውይይትን በማጎልበት፣ ሰላም ያላቸው ክልሎች እና አንድነትዋ የጠነከረ ኢትዮጵያን ለመገንባት ጊዜዎን፣ ጉልበትዎንና እውቀትዎን ያበርክቱ። የጋራ ስምምነትና መግባባት የሰፈነባት አገር መፍጠር እንችላለን።
  • በኢሜል contact@H4Peace.org ወይም ይህንን ቅጽ በመሙላት ያግኙን። ሙሉ አድራሻዎን እና የኛ ተነሳሽነትን ሊጠቅም የሚችል ያልዎት ማንኛውም ችሎታ፣ አስተዋጽኦና
    ፍላጎት ጨምረው ይግለጹ።