Phone:

666 888 0000

ኢሜይል:

contact@h4peace.org

የተስፋ ለሰላም ስብስብ መቋቋምን በተመለከተ የተሰጠ መግለጫ

 

መስከረም 28 ቀን 2016 ዓ.ም

የተስፋ ለሰላም ስብስብ መቋቋምን በተመለከተ የተሰጠ መግለጫ

“ተስፋ ለሰላም” ለዘመናት የኖረ ትስስርና ዝምድና ባላቸው የአማራና የትግራይ ማህበረሰቦች መካከል ያለው የእርስ በርስ ቅራኔና ግጭት አብዝቶ ባሳሰበንና ከሁለቱም ወንድማማችና እህትማማች ማህበረሰቦች ተወላጅ በሆንን ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የተቋቋመ የሰላም አጀንዳ አራማጅ ስብስብ ነው። ዓላማችንም በአማራና በትግራይ ማህበረሰቦች መካከል ባለፉት አመታት እየተባባሰ የመጣውና በተለይም በቅርቡ በተካሄደው ጦርነት ምክንያት የተፈጠረው ቅራኔ እንዲወገድና ወደተሻለ ሰላማዊ ግንኙነት እንዲቀየር ጥረት ማድረግ ነው።

ለ “ተስፋ ለሰላም” መፈጠር መነሻ የሆነው ዋናው ምክንያት በእነዚህ በሃይማኖት፣ በባህል፣ በስነ-ልቦና እና በታሪክ ረገድ የተጋመደ ማንነት ባላቸው ሁለት ተጎራባች ማህበረሰቦች መካከል የተፈጠረው የወቅቱ የከረረ ቅራኔ በረዥም ዘመን የግንኙነት ታሪካቸው ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ከፖለቲካ ልኂቃን አልፎ የሕዝብ-ለሕዝብ ቅራኔና ግጭት እየሆነ መምጣቱ ነው። ቅራኔው ሁለቱን ማህበረሰቦች ለከፍተኛ እልቂት የዳረገ ከመሆኑም በላይ ሀገራችንን ወደ ከፍተኛ የፖለቲካ ቀውስ ውስጥ እንድትገባ አድርጓታል። ይህ ከፍተኛ የፖለቲካ ቀውስም የአገሪቱንና የዜጎቿን ህልውና የሚፈታተን የውጭ ሃይሎች ጣልቃ ገብነትን ፈጥሯል።

በአሁኑ ጊዜ በአብዛኛው የኢትዮጵያ አካባቢዎች ማለትም – በትግራይ፣ በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በአፋር፣ በሶማሌ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በጋምቤላ ክልሎችና በሌሎችም አካባቢዎች – ከአነስተኛ ግጭቶች እስከ ከፍተኛ የእርስበርስ ጦርነት መካሄዱ በሚልዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎችን ህይወትና የአገሪቱን ህልውና ከፍተኛ አደጋ ላይ ጥሎታል። ከእነዚህ ጦርነት የተካሄደባቸውና እየተካሄደባቸው ከሚገኙ አካባቢዎች ውስጥም ለሁለት አመታት በሶስት ተከታታይ ዘመቻዎች በትግራይ ክልል በዋናነት እንዲሁም የትግራይ አጎራባች በሆኑት በአማራና በአፋር ክልሎች የተካሄደው፣ ላለፉት አራት ተከታታይ አመታት በኦሮሚያ ክልል የተካሄደውና እየተካሄደ ያለው፣ በአሁኑ ወቅትም በአማራ ክልል እየተካሄደ ያለው ጦርነት ከፍተኛ ድርሻ የሚይዙ ናቸው።

በተለይም በትግራይና በአማራ ክልሎች የተካሄደው ጦርነት የትውልዱን ህልውና መቀጠል ጥያቄ ውስጥ በሚያስገባ መጠን እጅግ ደም-አፋሳሽ እና አውዳሚ ሆኖ ታይቶል። ከዚህ በተጨማሪም በእነዚህ ሁለት ክልሎች መካከል የተካሄደው ጦርነት ባልተለመደ ሁኔታ የሕዝብ-ለሕዝብ የከረረ ቅራኔና ግጭት የታየበትና የውጪ ኃይሎች ከፍተኛ ጣልቃ-ገብነት ያለበት መሆኑም ችግሩን ይበልጥ ውስብስብ፣ አሳሳቢ እና የተለየ አድርጎታል። በአጠቃላይ ይህ ስብስብ እንዲፈጠር አስፈላጊ ሆኖ የተገኘው የወቅቱን ግጭቶች በዘላቂነት ለማስቆም በፕሪቶሪያና በናይሮቢ በቅርቡ የተደረሰው አበረታች የሰላም ስምምነት በዙሪያው የሚታዩ ጉድለቶች በአስቸኳይ ታርመው ተግባራዊ እንዲሆኑ ማድረግና በአሁኑ ወቅት በአማራ ክልል እየተካሄደ የሚገኘው ጦርነት በውይይትና በድርድር የሚፈታበት እድል እንዲፈጠር፣ ምናልባትም ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት ጦርነቱ የሚቀጥል ከሆነ በሕዝብ ላይ የሚደርሰውን አደጋ በመቀነስ ረገድ የሁለቱ ማህረሰቦች ግንኙነት ወደ በጎ አቅጣጫ መቀየር የማይተካ ሚና እንዳለው ስለታመነበት ነው።

የ “ተስፋ ለሰላም” ዋና ዓላማ በእነዚህ ሁለት ጥብቅ የጋራ ማንነት ባላቸው የአማራና የትግራይ ማህበረሰቦች ዘንድ የተፈጠረው የጥላቻ ስሜትና ግጭት በአስቸኳይ እንዲቆምና ግንኙነታቸው ወደ ጤናማና ሰላማዊ ሁኔታ እንዲመለስ የሚያስችል ጥረትና ግፊት ማድረግ፣ በሂደትም በሁለቱ ማህበረሰቦች ዘንድ ያሉትና ለችግሩ መፈጠር ምክንያት የሆኑ ፖለቲካዊም ሆኑ ሌሎች ቅራኔዎች በውይይት፣ በድርድር እና በሕጋዊ መንገድ የሚፈቱበት ሰላማዊ የፖለቲካ ምህዳር እንዲኖር የሚያስችል ጥረት ማድረግ ነው።

የ “ተስፋ ለሰላም” ሚና ችግሩን ለመፍታት በሚኖረው ሂደት ውስጥ የድርድር ተሳታፊ ወይም አደራዳሪና አሸማጋይ መሆን አይደለም። ይልቁንም በሁለቱ ማህበረሰቦች ዙሪያ የሚታየው የጥላቻና የበቀል ስሜት ያጠላበት ንግግርና ቅስቀሳ እንዲወገድ፣ ሕዝቡና የፖለቲካ ኃይሎች ልዩነቶቻቸውን በጦርነት ሳይሆን በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ የሚያስችል ጫና እንዲፈጠር፣ ሕብረተሰቡን እንወክላለን የሚሉ የፖለቲካ ኃይሎችም ቅራኔአቸውን በጦርነት ሳይሆን በጠረጴዛ ዙሪያ ውይይት፣ ድርድር እና በሕጋዊ መንገድ ብቻ እስከመጨረሻው ለመፍታት እንዲወስኑ የሚያስችል ጥረትና ግፊት እንዲኖር ማስቻል ነው።

“ተስፋ ለሰላም” የተባለው ይህ ስብስባችን ይህንን ዓላማውንና ሚናውን ስኬታማ ለማድረግ የሚያስችሉ ልዩ ልዩ ዝግጅቶችን ከአንድ አመት በላይ ሲያደርግ ቆይቷል። በዚህ የዝግጅት ሂደቱም ፥-

  • ለሁለቱ ማህበረሰቦች መቃቃርና ግጭት መነሻ የሆኑ መሰረታዊ ምክንያቶች ምን ምን እንደሆኑ፣
  • ችግሩ በአሁኑ ወቅት በምን ዓይነት የክብደት ደረጃ ላይ እንደሚገኝ፣
  • የሁለቱን ማህበረሰቦች የሕዝብ-ለሕዝብ ግንኙነት እንዴት ማጠናከር እንደሚቻልና
  • ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ያሉት የአጭርና የረዥም ጊዜ የመፍትሄ አማራጮች ምን ምን እንደሆኑ በጥልቀት በመገምገም በጉዳዮቹ ዙሪያ የጋራ መግባባት ላይ ለመድረስ ችሏል።

 

እንዲህ ዓይነቱን መግባባት መፍጠር የተፈለገውም በችግሩ መነሻ ምክንያቶችና በመፍትሄው ዙሪያ ጠንካራ ግንዛቤና መግባባት ካልተፈጠረ በስተቀር እንዲሁ በደፈናው “ችግሩ በሰላም ይፈታ” እያሉ መናገር ወይም ጥያቄ ማቅረብ ትርጉም ያለው ለውጥ ማምጣት እንደማያስችል ግንዛቤ በመወሰዱ ነው። ከዚህ በተጨማሪም ስብስቡ የተነሳበትን ዓላማ ለማሳካት ምን ምን ዓይነት ተግባራትን በቅደም- ተከተል ማከናወን እንደሚገባው ዝርዝር ዕቅድ ያወጣ ሲሆን ኃላፊነቱን በአግባቡ ለመወሰንና ለማስፈፀም የሚያስችለው አንድ የጋራ የመግባቢያ ሰነድ ማፅደቅም ችሏል። ሃላፊነቱን በአግባቡ ለመወጣት የሚያስችሉት ልዩ ልዩ ኮሚቴዎችም አቋቁሟል። ስብስቡ በቅርቡ በሚሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫም ራሱን በይፋ ለሕዝቡ ለማስተዋወቅ ዝግጅቱን እያጠናቀቀ ይገኛል።

“ተስፋ ለሰላም” በሁለቱ ማህበረሰቦች ዘንድ የተፈጠረው ችግር መነሻውም ሆነ የወደፊት መፍትሄው በዋናነት ፖለቲካዊ ይዘት ያለው መሆኑን ቢገነዘብም ስብስባችን የሁለቱን ማህበረሰቦች ግንኙነት ወደ ሰላማዊና ጤናማ ግንኙነት ለመቀየር የሚያስችል ጥረትና እገዛ ከማድረግ ባለፈ ከፖለቲካ ሥልጣን ጥያቄ ጋር የተያያዘ ምንም ዓይነት የፖለቲካ አጀንዳና ተልዕኮ የለውም። ስለሆነም ተስፋ ለሳላም በጊዚያዊነት የተቋቋመ የሰላም ስብስብ መሆኑን ከወዲሁ ለማሳወቅ እንወዳለን። ስብስቡ የተቋቋመበት ዓላማ ውስንና ጊዜያዊ መሆኑን በመገንዘብም “ተስፋ ለሰላም” ቋሚ መዋቅርና ሕጋዊ እውቅና እንዲኖረው ሳያስፈልገው ውስን ዓላማውን ለማስፈፀም በሚያስችለው አግባብ ብቻ የሚንቀሳቀሰ ይሆናል።

በሁለቱ ማህበረሰቦች መካከል የተፈጠረውን የወቅቱን ችግር ለመፍታት የሚያስችል ጥረትና እገዛ ማድረግ በራሱ ጠቃሚና ከፍተኛ ግብ ቢሆንም ዞሮ ዞሮ የችግሩ መነሻም ሆነ መድረሻ ከአጠቃላዩ የሀገሪቱ ሕዝብ ጥቅምና ፍላጎት ሙሉ በሙሉ ተነጥሎ ሊታይ አይችልም። ስለሆነም የተነሳንበት ዓላማ ስኬታማ እንዲሆን የሁሉም የኢትዮጵያ ማህበረሰቦች ተሳትፎና እገዛ የግድ አስፈላጊ ይሆናል። የተስፋ ለሰላም ስብስብ ዋና ትኩረት የአማራና የትግራይ ህዝቦችን ማቀራረብ ቢሆንም፣ በእነዚህ ሁለት ማህበረሰቦች መካከል የተፈጠረው ቅራኔ ከእነርሱም አልፎ ሀገራዊ እና አካባቢያዊ (ቀጠናዊ) አንደምታው ምን ያህል ከባድና አሳሳቢ እንደሆነ የሚገነዘቡ የሌሎች ብሔር ተወላጆችም በሂደት “የተስፋ ለሰላም” ተሳታፊ የሚሆኑበትን ዕድል ማመቻቸት አስፈላጊ መሆኑን ታሳቢ በማድረግ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።

የክብደት ደረጃው ቢለያይም በሌሎች ተጎራባች በሆኑ የሀገሪቱ ክልሎች ዙሪያም (በተለይም በአማራና በኦሮሚያ) እያቆጠቆጡ ያሉ ተመሳሳይ የሕዝብ-ለሕዝብ ቅራኔዎች እየታዩ ስለሆነ ሌሎች የ“ተስፋ ለሰላም” ዓይነት ስብስቦች በተመሳሳይ ሁኔታ እየተቋቋሙ ቅራኔዎቹ የበለጠ ከመጠናከራቸውና ከመወሳሰባቸው በፊት መፍትሄ እንዲያገኙ መጣር ተገቢ ነው ብለን እናምናለን። የሕዝብ ለሕዝብ ግጭቶች በባህሪያቸው በመንግሥትና በፖለቲካ ድርጅቶች አማካኝነት ብቻ የመፈታት ዕድላቸው የጠበበ ስለሆነም መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ጥረትና ተሳትፎ የበለጠ ሊጠናከር ይገባዋል።

በአጠቃላይ በማህበረሰቦች መካከል የተፈጠረን አንድን ቅራኔ ወይም ግጭት መፍታት የማንንም ሌላ ወገን ጥቅም የማይነካና ይልቁንም ለሁሉም የሀገሪቱ ማህበረሰቦች የሚጠቅም የጋራ አጀንዳ መሆኑን በመገንዘብ የ“ተስፋ ለሰላም”ን ዓላማ ሁሉም የኢትዮጵያ ማህበረሰቦች በቅንነት ሊያዩትና ሊደግፉት ይገባል። ሰላማዊ የማህበረሰብ ግንኙነቶች ለሀገርና ለሕዝብ ዘላቂ ሰላም መስፈን የማይተካ ሚና ያላቸው መሆኑን በመረዳትም የአማራና የትግራይ የክልል መንግሥታት፣ የፌደራሉ መንግሥት፣ የሰላም ደጋፊ የሆኑ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ተፅዕኖ-ፈጣሪ ግለሰቦች፣ የሲቪክ ተቋማትም ሆኑ ለተነሳንበት ዓላማ ደጋፊ የሆኑ ሰላም ወዳድ ዜጎች ለሃሳቡ ድጋፍ ከመስጠት ጀምሮ አብረውን በጋራ እንዲሰሩ ጥሪያችንን እናቀርባለን። የመገናኛ ብዙኃንና ማህበራዊ አንቂዎችም የ“ተስፋ ለሰላም” መልዕክቶች የጉዳዩ ባለቤት ለሆነው ሕዝብና ለተለያዩ ባለድርሻ አካላት በአግባቡ እንዲደርሱ በማድረግ ረገድ የየበኩላቸውን ድጋፍና ትብብር እንዲያደርጉልን በዚህ አጋጣሚ በአክብሮት እንጠይቃለን።

 

ተስፋ ለሰላም፣ ሰሜን አሜሪካ

ሰላም ለህልውናችን!

 

Search
Social Share